ሦስት(lll)

szosetelll

መስቀል እና ዳመራ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ዳራ ያለው በዓል ነው። ማህበራዊ መስተጋብሩ፣ ግርግሩ ሁሉ ይለያል። እኔን የገረመኝ ነገር በሀይማኖታችን ያለውን አስተምህሮ ወደ ባህላችን አስርገን፣ በትውፊቶቻችን ውስጥ አካተን አመስጥረን እንዴት እንደተጠቀምንባቸው ነው። ይህችን እፍኝ የማትሞላ ፅሁፍ እንዲሁ ስለወደድኳት ላጋራችሁ።

ሦስት(lll)

በየአመቱ በሰፈራችን ዳመራ እንደምራለን። ከአመቱ ደርሰን ከግቢያችን ውጪ ችቦ ይዘን ዳመራ ጋር ቆመናል። እማወራዎች ቤታቸው ያፈራውን አምባሻ፣ ድፎ፣ ባቄላ ይዘው ደርሰዋል። እንስቶች ቡና ያፈላሉ። አባወራዎች አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠው ያወጋሉ። አብዛኛው ሰው መምጣቱ ካታወቀ በኋላ አንድ አባወራ ከሰሜን አቅጣጫ  አንዷ እማወራ ደግሞ ከደቡብ አቅጣጫ ችቦ ለኩሰው መጡ። የተለኮሰውንም ችቦ ለሦስት አባወራዎች አስረከቡ። እነሱም(አባወራዎቹም) ችቦውን በእጃቸው ይዘው ዳመራውን ሦስት ጊዜ ዞሩ። ይህ ነገር ስላልገባኝ አጠገቤ የነበረውን ጎረቤቴን ይህን ጠየቅኩት። እኔ:- "ለምንድን ነው 3ቱ አባወራዎች 3 ጊዜ የዞሩት አልኩት።

እርሱም "ታቦትስ ሦስት ጊዜ ዞሮ አይደል ወደ መቅደስ 'ሚገባው" አለኝ። ይህን ሲለኝ ይህ ሁናቴ ሀይማኖታዊ ዳራ እንዳለው ተረዳሁ። ይህም ሦስትነት የሥላሴ ምሳሌ እንደሆነ። ሶስትነትን ከሀይማኖት ባለፈ በየዕለት ትውፊቶቻችንና ንግግራችን ምናዘውትረው ነገር ይመስላል። ለምሳሌ:- ነገር በሶስት አይፀናም እና ወዘተ...ሌላም አባባል ይኖራል።

ይህንንም ስናወራ ዳመራው ተቀጣጥሎ አልቆ ቋሚው(ምሰሶው) ብቻ ቆሟል። ሰውም የመውደቁን ሁኔታ ለመከታተል ከያለበት ይጠባበቃል። እርሱ ግን እንዲሁ በቀላሉ አይወድቅም።  ሳይታሰብ ግን ወደ ሰሜን ወደቀ። ሰውም እሰይ በሰሜን አዝዕርቱ ፍሬ ያፈራል፣ ያሸታል አሉ። ዳቦውም፣ ባቄላውም ከተበላ ቡናውም ከተጠጣ በኋላ የምርቃቱ ተራ ደረሰ። 3  መራቂዎች ተመርጠው 3 ጊዜ መረቁ። ቅድም የጠየኩትን ጎረቤቴን ምርቃቱም ሶስት ነው አልኩት። እርሱም- አይ አንተ አስተውለኸዋል ግን ዛሬ ጥያቄ አብዝተሃል ምነው አባትህ ስለዚህ ነገር አያስረዳህም ብሎኝ አባቴን በጨረፍታ ሲያየው እኔም ሳቅ አልኩና በሃፍረት አንገቴን አቀረቀርኩ።

መስከረም ፳፻፩፯

Comments (0)
No comments yet